ከሰሞኑ የዲያስፖራዉ ማህበረሰብ ሁለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካዉንቶችን በመጠቀም ለወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮች ድጋፍ እንዲያደርግ በማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት ጥሪዎች ሲቀርቡ ተመልክተናል።

እነዚህ አካዉንቶች ‘Ministry of Foreign Affairs – National Cause’ በሚል ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከፈቱ (ዶላር አካዉንት፡ 1000439142786 እና ዩሮ አካዉንት፡ 1000439142832) እንደሆኑም ተጽፏል።

በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም ስለ ባንክ አካዉንቶቹ ምንነትና ትክክለኛነት እንድናጣራ ጠይቀዉናል።

ኢትዮጵያ ቼክም የነዚህን ሁለት የባንክ አካዉንቶች ምንነትና ትክክለኛነት በተመለከተ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ ዲፕሎማት የሆኑትን አቶ ነብዩ ሰለሞንን አናግሯል።

እርሳቸዉም እነዚህ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋሩ የሚገኙት ሁለት አካዉንቶች ትክክለኛና ህጋዊ መሆናቸዉን ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በዉጭ ሀገራት ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለሀገራዊ ጉዳይ (National Cause) ልገሳ ለማሰባሰብ በእጅ ስልኮች ላይ የሚጫን መተግበሪያና በበይነ መረብ የታገዙ ሀብት ማሰባሰቢያ ስልቶችን ‘ቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ’ ከተባለ ሀገር በቀል ኩባንያ ጋር በመተባበር ተግባራዊ ማድረጉንም አቶ ነብዩ ሰለሞን ንግረዉናል።

ይህ አይዞን ኢትዮጵያ (‘eyezon’ https://eyezonethiopia.com/) የተሰኘ መተግበሪያም የሀብት ማሰባሰቡን ስራ የሚያቀላጥፍና ለዲያስፖራዉ ማህበረሰብ ተደራሽ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ዲያስፖራዎች አይዞን ኢትዮጵያ መተግበሪያን በመጠቀም ካሉበት በክሬዲት ካርድ አማካኝነት ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚያበረታቱ የነገሩን አቶ ነብዩ ሰለሞን የባንክ አካዉንቶቹ እንደ ተጨማሪ አማራጭ የልገሳ ዘዴ የቀረቡ መሆኑን ነግረዉናል።

በአሁኑ ሰዕትም የዶላርና ዩሮ አካዉንቶቹ (ዶላር አካዉንት፡ 1000439142786 እና ዩሮ አካዉንት፡ 1000439142832) ስራ መጀመራቸዉንና የፓዉንድ አካዉንት ዝግጅት ድግሞ በሂደት ላይ መሆኑን አቶ ነብዩ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

በተጨማሪም አሁን ላይ በአይዞን ኢትዮጵያ አማካኝነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየተሰባሰበ እንደሚገኝና በቀጣይም አይዞን ኢትዮጵያ የዲያስፖራዉ ማህበረሰብ ለተለያዩ ጉዳዮች ድጋፍ የሚያደርግበት አሰራር መሆኑንም ነግረዉናል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የአይዞን ኢትዮጵያ መተግበሪያ እንዲሁም የዶላርና ዩሮ አካዉንቶቹን በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች እንዲሁም ፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሀብት ማሰባሰብ ላይ ለሚሰሩ የዲያስፖራ ስብስቦች ማሳወቃቸዉንም አቶ ነብዩ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::