ከሰሞኑ በብዛት እየተከፈቱ ካሉ ሀሰተኛ የትዊተር አካውንቶች ይጠንቀቁ!

ሰሞኑን በርካታ የትዊተር አካውንቶች በታዋቂ ግለሰቦች ስም እየተከፈቱ ይገኛሉ፣ ለዚህም “አካውንቴ ተዘግቶብኝ/ጠፍቶብኝ አዲስ ከፍቻለሁ” እንዲሁም “ከዛሬ ጀምሮ ትዊተርን ተቀላቅያለሁ” የሚሉ ምክንያቶችን ይሰጣሉ።

በትክክል በነዚህ ምክንያቶች አዳዲስ አካውንቶችን እየከፈቱ ያሉ ግለሰቦች ሊኖሩ ቢችሉም በርከት ያሉ ሀሰተኛ አካውንቶችም እየተከፈቱ እንደሆነ አስተውለናል።

እነዚህን ተመሳስለው የሚከፈቱ አካውንቶችን ላለመከተል እነዚህን ነጥቦች ልብ ይበሉ:

– የአካውንቱ ባለቤትን ትክክለኛ/የቀደመ አካውንት የሚያውቁ ከሆነ መዘጋቱን ወይም ትዊት ማረግ ማቆሙን ያረጋግጡ

– አካውንቱ የተከፈተበትን ግዜ ይመልከቱ

– በአካውንቱ ላይ የሚቀርቡ መልዕክቶችን ይመርምሩ፣ ፅሁፎችን በራሱ ያቀርባል ወይስ የሌሎችን በብዛት ሪትዊት ያደርጋል?

– ግለሰቡ የፌስቡክ ወይም ሌላ አካውንት/ገፅ ካለው እዛ ላይ ከሚፃፈው ጋር ተመሳሳይ/ተቃራኒ መሆኑን ልብ ይበሉ

– አካውንቱን የሚከተሉትን ግለሰቦች እና ድርጅቶች ይመልከቱ፣ የተከታዮቹን ብዛትም ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ

– በአካውንቱ ላይ የሰፈረውን የፕሮፋይል መረጃ (ፎቶ፣ ድረ-ገፅ፣ ስራ ወዘተ) በአፅንኦት ይመልከቱ

ከነዚህ ውስጥ አንዱ ብቻውን ሀሰተኛ የትዊተር አካውንትን ለመለየት በቂ ላይሆን ይችላል፣ ነገር ግን ሁሉም በአንድነት ሲቃኙ ፍንጮችን ሊሰጡ ይችላሉ።

አንዳንድ ጥናቶች ትዊተር ላይ ካሉት አካውንቶች መሀል 4% የሚሆኑት ሀሰተኛ እንደሆኑ ይጠቁማሉ። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ትዊተር ላይ የሚከተሏቸውን አካውንቶች በጥንቃቄ ይምረጡ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::