ከሰሞኑ በስፋት ተግባር ላይ እየዋለ ካለ ከዚህ የማጭበርበርያ ዘዴ ይጠንቀቁ!

ከሰሞኑ በርካታ ተከታታይ ላላቸው እንዲሁም ቬሪፋይድ ለሆኑ የፌስቡክ ገፆች በምስሉ ላይ የሚታየው የማጭበርበርያ መልዕክት እየተላከ ነው። ድርጊቱ እንዴት ይከናወናል?

በመልእክቱ ላይ እንደሚታየው በሳምንት ሰባት ማስታወቂያ በገፃችሁ ላይ እናቅርብ እና 1,750 ዶላር እንክፈላችሁ የሚል መልዕክት ይላካል። በዚህ ተስማምቶ የሚቀጥል ግለሰብ ወይም ድርጅት ሲያገኙ ኤሜይል አስከትለው ይጠይቃሉ። ከዛም በኢሜይሉ አንድ የፌስቡክ ሊንክ ይልኩና “ይህን ሊንክ በመጠቀም የማስታወቂያ ድርጅቱን ይቀላቀሉ” ይላሉ።

እንግዲህ ማስተዋል ያለብን እዚህ ላይ ነው፣ እዚህ ሊንክ ላይ username እና password ካስገባን አጭበርባሪዎቹ ገፁን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ ፈቀድንላቸው ማለት ነው። ከዛም የገፁን ባለቤት አስወጥተው በራሳቸው ቁጥጥር ውስጥ ያረጉታል።

በዚህ ድርጊት ላለመጭበርበር ለሌሎች ሰዎች ወይም ድርጅቶች የማህበራዊ ሚድያ ገፆችን እና አካውንቶችን መጠቀሚያ ቃላቶች አሳሳፎ መስጠት አይገባም።

ከላይ የተጠቀሰው የአጭበርባሪዎች (scammers) ድርጊት ሲሆን ጠላፊዎችም (hackers) ተመሳሳይ ድርጊት ላይ ይሳተፋሉ። ከዚህ ለመዳን ደግሞ እነዚህን አምስት ቀላል ዘዴዎች እንጠቀም:

1. ሁልግዜ 2 factor authentication እንጠቀም

2. በቀላሉ ሊገመቱ የማይችሉ ጠንካራ ፓስወርዶችን እንጠቀም

3. ለገፃችን የምንጠቀመውን ኢሜይል ለማህበራዊ ሚድያ መግቢያ ከምንጠቀመው እንለይ

4. ፓስወርዳችንን ቢያንስ በየስድስት ወሩ እንቀይር

5. Username እና Password በአንድ ወይም አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ብቻ እንዲያዝ እናድርግ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::