ከሁለት ሳምንት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተላከው 3 ሺህ ኩንታል እህል ለተፈናቃይ ዜጎች እስካሁን ለምን አልደረሰም?

ታህሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሆን እርዳታ መላኩ ይታወሳል። ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲደርስ የተላከው 8.6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 3 ሺህ ኩንታል እህል በአሶሳ ዞን ሆሞሻ ወረዳ በሚገኝ መጋዝን እንዲራገፍ መደረጉን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እና በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ የቅሬታ ድምጾች ተሰምተው ነበር።

በወቅቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ታረቀኝ ታሲሳ በክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ በኩል ምላሽ የሰጡ ሲሆን ችግሩ የተፈጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እርዳታውን ወደ አሶሳ ይዞ በመምጣቱና የተሽከርካሪዎች ኮንትራት እስከ አሶሳ ብቻ በመሆኑ እንዲራገፍ መደረጉን ገልጸው ነበር። ኮሚሽነሩ እርዳታውን ወደ መተከል ለማጓጓዝ “የፀጥታ ችግር ያለበት ስለሆነ ለማሳጀብ ከሚመለከተዉ አካል ጋር እየተናጋገርን ነው” ብለውም ነበር።

ለተፈናቃዮች እንዲደርስ ተብሎ ከ2 ሳምንት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተላከው 3 ሺህ ኩንታል እህል አሁን ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ኢትዮጵያ ቼክ የክልሉን ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽቤት ሀላፊ አቶ መለስ በየነን አነጋግሯል።

አቶ መለስ የእርዳታ እህሉ አሁንም በሆሞሻ ወረዳ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ታሽጎ መቀመጡን ለኢትዮጵያ ቼክ የገለጹ ሲሆን ለዚህም ከአሶሳ ወደ መተከል በሚወስደው መንገድ ያለውን ከፍተኛ የጸጥታ ችግር በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

በክልሉ የተቋቋመው የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ እህሉን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ለተፈናቃዮች ለማድረስ መወሰኑን የገለጹት አቶ መለስ ረጅሙን የአሶሳ-ቡሬ-መተከልን መንገድ በአማራጭነት ለመጠቀም ስለመታሰቡም ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::