ጥቂት ስለ ትዊተር አጠቃቀም እና በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል!

በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ትዊተርን በመቀላቀል በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ዘመቻዎች ሲከውኑ አስተውለናል። ብዙዎቹ ትዊተርን ከመቀላቀላቸው በፊት የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ አክቲቪስቶች መገልገያውን እንዴትና ለምን መጠቀም እንዳለባቸው ገለጻ ሲሰጣቸው መመልከት ችለን ነበር። 

ገለጻዎቹ በፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት እንዲሁም እንደ ዋትስአፕ ባሉ መተግበሪያዎች ይከወኑ ነበር። ገለጻዎቹን ተከትሎም በርከት ያሉ ተጠቃሚዎች በብዛት ትዊተርን የተቀላቀሉ ሲሆን ፋታ በማይሰጡ ዘመቻዎችም ሲሳተፉ ታይቷል። 

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ የመንግስት ሚዲያዎች ስለትዊተር አጠቃቀም የሚገልጹ መርሃ-ግብሮችን ሲያሰራጩ ተመልክተናል። ለምሳሌ ኢቢሲ ይህንኑ የተመለከተ መርሃ-ግብር ከሰዐታት በፊት ለተመልካቾቹ ሲያጋራ ተመልክተናል። በነገራችን ላይ ኢቢሲ ባሰራጨው መርሃ-ግብር የትዊተር የቦታ ምጣኔ ፊደላት 140 መሆኑን የሚገልጽ ይዘት ያስቀመጠ ሲሆን ይህ የተሳሳተ ነው። ትዊተር ከሶስት ዓመት በፊት የቦታ ምጣኔውን ከ140 ወደ 280 ከፍ ማድረጉ ይታወቃል። 

ብዙ ሰዎች ትዊተርን መቀላቀላቸው ለመረጃ ቅርብ እንዲሆኑና የሚደግፉትን ሀሳብ በነጻነት እንዲያሰራጩ እንዲሁም ሀሳባቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ግፊት ለማድረግ ያስችላቸዋል። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ከሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች እራሳቸውን እንዲያርቁ ኢትዮጵያ ቼክ የሚመክር ሲሆን የትዊተርን ፖሊሲ ማክበርም አካውንታቸው ዘለቂታ እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን። 

በትዊተር ፖሊሲ መሰረት ተጠቃሚዎችን ሊያደናግር የሚችል ሀሰተኛ አካውንት መክፈት፣ የተሰረቁ እንዲሁም አሳሳች የፕሮፋይል ፎቶዎችን መጠቀም፣ የተኮረጀ ወይንም የተሰረቀ ባዮግራፊ መጻፍ፣ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ የተለያዩ ከአንድ በላይ አካውንቶችን መክፈት፣ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ትዊቶች መለጠፍ ወዘተ የተከለከሉ ናቸው። 

ስለትዊተር ፖሊሲ በዝርዝር ለማወቅ የሚከተለውን ሊንክ ይከተሉ: https://help.twitter.com/en/rules-and-policies/platform-manipulation

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::