5G ቴክኖሎጂ ካንሰር ያስከትላል፣ ኮሮና ቫይረስ ያስተላልፋል ወዘተ የሚሉት ሴራ ትንተናዎች እውነትነት አላቸው? 

ኢትዮ ቴሌኮም በትናንትናው እለት የ5G ሞባይል ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ጣቢያዎች ማስጀመሩን አስታውቋል። 

 

ይህ አምስተኛዉ ትዉልድ የሞባይል ኔትዎርክ ለግለሰቦችም ሆነ ተቋማት በርካታ እድሎችን እየፈጠረ ያለ፣ ለተገልጋዮችም የላቀ ተሞክሮን ያመጣ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ይነገራል። 

 

5Gን በቴክኖሎጂ ከበለጸጉ ሀገራት እንደ ቻይና፤ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ከአፍሪካም ኬንያና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እየተጠቀሙት ይገኛሉ። 

 

ይህ ኔትዎርክ በበርካታ መመዘኛዎች አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ከሚገነዉ 4G ኔትዎርክ የተሻለና አስተማማኝ ነዉ። 

 

ለአብነትም 4G ኔትዎርክ ከ3G እና 2G የተሻለ የሞባይል አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም 5G ኔትዎርክ ግን ከ4G ኔትዎርክ እስከ 100 እጥፍ ፈጣን ሊሆን ይችላል። 

 

የ5G ኔትዎርክ ይህ ፍጥነት እስከ 20 Gbps ይደርሳል። ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን /latency/ የሚቀንስም ነዉ። 

 

እንደ ምሳሌም አንድ ሙሉ HD ጥራት ያለዉን ፊልም በሰከንዶች ዉስጥ ማዉረድ /download/ ማድረግ ያስችለናል ማለት ነዉ። 

 

በተጨማሪም 5G ኔትዎርክ ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸዉ ግንኙነቶች /mission-critical communications/ እና ሴንሰርና ሶፍትዌር ያላቸዉ አካላት በኢንተርኔትም ሆነ በሌላ መገናኛ ዘዴዎች እንዲገናኙና በተቀላጠፈ መልኩ መረጃ እንዲለዋወጡ /Internet of Things/ ያስችላል። 

 

የትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግን ጨምሮ ጤና፤ ግብርና፤ ሎጂስቲክስና ሌሎች ዘርፎች እንዲዘምኑ በማድረግ ረገድም 5G ኔትዎርክ ከፍተኛ ሚና አለዉ። 

 

የዚህ ቴክኖሎጂ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ መዋል በቴሌኮም ኦፕሬተሮች፤ ይዘት ፈጣሪዎች /content creators/፤ መተግበሪያ አበልጻጊዎች እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል በሚፈጥረዉ የገበያ ትስስር ብቻ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይታሰባል። 

 

ይሁን እንጂ 5G ኔትዎርክ ከጥርጣሬ፤ ነቀፋና ሴራ ትንተናዎች የጸዳ አይደለም። 

 

5G ኔትዎርክ፤ ካንሰርና ኮሮናቫይረስ

 

5G ኔትዎርክ ላይ ሲቀርቡ ከቆዩ ተቃዉሞዎች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂዉ የሰዉ ልጆችን ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል የሚል ነዉ። 

 

ከነዚህ መካከልም 5Gን ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የሬድዮ ሞገዶች ካንሰርን እንዲሁም ኮሮናቫይረስን ያመጣሉ ወይም የሰዉነታችንን ቫይረሱን የመቋቋም አቅም ይቀንሳሉ የሚሉ ይገኙበታል። 

 

የዚህ ሴራ ትንተና አራማጆችም በተለያዩ የአለም ሀገራት ተቃዉሞ ሲያሰሙ እንዲሁም የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ተመልክተናል። 

 

“ኮሮናቫይረስ የተፈጠረዉ ሰዎች በቤታቸዉ እንዲቆዩና ኢንጂነሮች ያለ ምንም ተቃዉሞ የ5G ኔትዎርክን በየቦታዉ እንዲዘረጉ ነዉ” የሚሉም አልጠፉም።

 

ይሁን እንጂ እነዚህ 5G ኔትዎርክን የተመለከቱ ሴራ ትንተናዎች በማስረጃዎች የታገዙ አይደሉም።

5Gን ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የሬድዮ ሞገዶችን የጤና ተጽኖ በተመለከተም ምንም የሚያሳስብ ነገር እንደሌለ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። 

 

በተጨማሪም የአለም ጤና ድርጅት 5G ኔትዎርክና ኮሮናቫይረስን በተመለከተ በ2020 ባሰራጨዉ መልዕክት ኮሮናቫይረስ በሬድዮ ሞገድ አማካኝነት እንደማይጓዝ/እንደማይሰራጭ ተናግሯል። 

 

ቫይረሱ 5G ኔትዎርክን በዘረጉ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂዉ በሌላቸዉ በርካታ ሀገራትም እየተሰራጨ መሆኑን አስነብቦ ነበር: https://www.who.int/multi-media/details/covid-19-5g-mobile-networks-do-not-spread-covid-19/

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::