20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች በዛሬዉ እጣ ያልተካተቱት ለምንድን ነዉ?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲያስገነባቸው የቆየዉን የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ የማዉጣት ስነስርዓት ዛሬ አካሂዷል። 

ይሁን እንጂ በ20/80 ፕሮግራም ባለ ሶስት መኝታ ቤት የ1997 ተመዝጋቢዎች በእጣዉ ያለመካተት በርካቶች ዘንድ ብዥታን የፈጠረ መሆኑን ተመልክተናል። በርካታ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታዮችም ስለጉዳዩ መረጃ ጠይቃችሁናል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ፌስቡክ ገጽ መረዳት እንደቻለዉ በዛሬዉ እለት እጣ ከወጣባቸዉ 25491 ቤቶች ዉስጥ 18648ቱ የ20/80 ፕሮግራም ቤቶች ናቸዉ። እነዚህ 18648 ቤቶች ደግሞ ስቱድዮ፤ ባለአንድ መኝታ ቤት እና ባለሁለት መኝታ ቤት ናቸዉ። 

ስለዚህም ባለ ሶስት መኝታ ቤት የ1997 ተመዝጋቢዎች በእጣዉ አልተካተቱም ማለት ነዉ። 

የከተማ አስተዳደሩየባለ ሶስት መኝታ ቤት በተመለከተ ፕሮግራሙ ባለፈዉ ዙር በቦርድ ዉሳኔ በመዘጋቱ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናልሲል በፌስቡክ ገጹ ጽፏል። 

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት የ1997 20/80 ተመዝጋቢዎች በ12ኝዉ ዙር እጣ መመሪያዉ ከሚጠይቀዉ የ60 ወር ቁጠባ ወርዶ 1500 ብር የቆጠቡት ጭምር በእጣ መካተታቸዉን ለሚዲያዎች በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል። 

12ኛ ዙር ላይ ቦርዱ መመሪያ አስተላልፎ፤ ቃለጉባኤ ይዞ፤ ወስኖ እስከ 1500 ድረስ ወርዶ ፈቀደላቸዉ። ከዛ በኋላየመጨረሻ እስከ 1500 ወርደናል ባለ ሶስት መኝታ አልቋልበሚል አናዉንስ ተደረገብለዋል። 

ይሁን እንጂ የ20/80 ፕሮግራም ቢዘጋም ጥቂት ሰዎች የባንክ ቁጠባ አካዉንታቸዉን ሳይዘጉ መቆጠብ መቀጠላቸዉን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል። 

በዛሬዉ የእጣ ስነስርዓት ያልተካተቱትም እነዚህ 20/80 ተመዝጋቢዎች ሲሆኑ ለወደፊት በሌላ መንገድ እንደሚስተናገዱም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

አሁን አጠቃላይ ነገሩን ከምናበላሸዉና ሲስተሙንም እንደገና ከምንደበላልቀዉ ጥቂት ስለሆኑ በዚህ እጣ ዉስጥ አይካተቱ ነገር ግን ከባንክ በወሰድነዉ መረጃ መሰረት እስከ የካቲት 21 (2014) ቆጥበዉ ብቁ የሆኑትን በሌላ መንገድ እናስተናግዳቸዋለንብለዋል።

ፎቶ: የከንቲባ ፅ/ቤት

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::