አትሌት ለተሰንበት ግደይ በቶክዮ ኦሎምፒክ ላትሳተፍ ትችላለች?

በቅርቡ የ5,000 ሜትር ሪከርድን ስፔን፣ ቫሌንሽያ ላይ የሰበረችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ በመጪው ቶክዮ ኦሎምፒክ መሳተፏ አጠራጣሪ እንደሆነ የሚገልፁ የተለያዩ መልእክቶች ከትናንት ጀምሮ ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተላለፉ ይገኛሉ። እነዚህ መልእክቶች አክለውም ኑሮዋን እና የአትሌቲክስ ልምምዷን በትግራይ ክልል ያደረገችው ለተሰንበት “የፖለቲካ አለመረጋጋት ሰለባ” እንደሆነች እና ከዋናው ብሄራዊ ቡድን ልትለይ እንደምትችል አስነብበዋል።

የአትሌቷ አሰልጣኝ ሀይሌ እያሱ መረጃው የሀሰት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግሮ “ለተሰንበት በደንብ ኦሎምፒክ ላይ ትሳተፋለች፣ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተደረገልን ጥሪ መሰረት ያለፈው ሰኞ እለት አዲስ አበባ መጥተናል፣ አትሌት ደራርቱም ተቀብላናለች። አሁን ሁሉም እንደሚያደርገው የኮቪድ ምርመራ አርጋለች፣ ውጤቱ እንደታወቀ ቡድኑን ትቀላቀላለች” ብሏል።

“በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት የአትሌቷ ልምምድ ተስተጓጉሎ ይሆን?” የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ቼክ የቀረበለት አልጣኝ ሀይሌ “በነበረው ችግር ምክንያት አርፍደን መጥተናል። እኛ የነበርነው ደቡባዊ ትግራይ አካባቢ ነበር፣ ከሌላው አካባቢ በአንፃራዊ የነበረው ሁኔታ ይሻል ነበር። ግን ልምምዷን ለተወሰነ ግዜ አቋርጣ ነበር። አሁን ግን ጀምሯለች፣ ሌላ ምንም ችግር የለም፣ ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚነገረው ውሸት ነው” ብሏል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ይህንን ዛሬ ያረጋገጠ ሲሆን አትሌት ለተሰንበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቡድንን ለመቀላቀል የኮቪድ ውጤት እየጠበቀች እንደሆነ አስታውቋል።

“ሀጎስ ገ/ህይወትን ጨምሮ ሌሎች በትግራይ ክልል ክለቦች ውስጥ የነበሩ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ለዝግጅት ሆቴል ከገቡ 15 ቀን አልፏቸዋል” ያለው ኮሚቴው ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ከ8 ወር በፊት አስቀድሞ አትሌቶችን በመጥራት ለዝግጅት ሆቴል እንዳስገባ አስታውቋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::