የአርብ የሚድያ ዳሰሳ

  1. በአርትስ ቲቪ የ”አበስኩ ገበርኩ” ፕሮግራም አዘጋጅ እንዳልካቸው ዘነበ በጋሞ ዞን በብርብር ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኝ በያዝነው ሳምንት ተሰምቷል። እንዳልካቸው “ሀሰተኛ መረጃ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጭተሃል” የሚል ክስ ቀርቦበት በጋሞ ዞን በብርብር ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። አርትስ ቲቪ ጉዳዩን ከያዙት ፖሊስ ባደረገው ማጣራት እንዳልክ የከተማዋን ከንቲባ ሥም የሚያጠፋን ጽሁፍ “ላይክ” እና “ሼር” አድርገሃል በሚል ክስ እንደቀረበበት ገልጿል፡፡ ይህንን ክስ ግን እንዳልካቸው እና ቤተሰቦቹ እንደማይቀበሉትም በመግለጽ፤ ይልቁንስ ጉዳዩ የግል ቁርሾ መወጣጫ ነው ማለታቸውን አስታውቋል። በእንዳልክ ላይ በቀረበበት ክስ ወንድሞቹ ቴዎድሮስ ዘነበ እና ተከተል ዘነበ በአንድ መዝገብ እንደተከሰሱ የእንዳልካቸው እናት ተናግረዋል ብሎ አዲስ ማለዳ ዘግቧል።
  1. በሌላ ዜና፣ በጋሞ ዞን በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ሀሰተኛ መረጃን የማሰራጨት ወንጀልን የመከላከልና የእርምት እርምጃ የመውሰድ ስራ እየሰራ መሆኑን የምዕራብ ዓባያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል። የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ኢንስፔክተር ኢሳይያስ ጫማ እንደገለጹት “አሁን አሁን በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች የህዝብን አንድነትና አብሮነትን የሚያሻክሩና የግለሰቦችን ስብዕና የሚነኩ ስም የማጥፋት እንዲሁም ዛቻ የተቀላቀለበት መልዕክቶች ተበራክተዋል” ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌክ አካውንት ለማጣራት እየተሰራ ባለበት ሁኔታ አንድ የፖሊስ አባል ጠንቃቃ፣ ገለልተኛ ፣ ለአንድ ወገን ውግንና የማይሰጥ መሆኑ እየታወቀ እንዲሁም ውክልናና ስልጣን በሌለበት ሁኔታ የተቋሙን ገጽታ በሚያበላሽ መልኩ መረጃ ተላልፎ በመገኘቱ የወረዳው ፖሊስ የዲስፕሊን ክስ እንዲመሰረት አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል።
  1. “የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ኦመር የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው” ተብሎ ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚድያ የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብሎ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በትናንትናው እለት አስታውቋል። ከሰሞኑ አቶ ሙስጠፌ “የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው” የሚለው መረጃ የወጣው “ቢኪ” የሚባል ቦታ በሄዱበት ወቅት ነው። ሌላኛው ደግሞ፤ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ወደዚሁ “ቢኪ” የተባለ ስፍራ በሄዱበት ወቅት ወጣቱን ጨምሮ ህብረተሰቡ በመቆጣቱ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበርና ድንጋይም እስከመወርወር የደረሰ ክስተት እንደተፈጠረ የሚገልፅ መረጃ ተሰራጭቷል። በክስተቱ ዙርያ ግን ምንም ማብራርያ እንዳልተሰጠ ቲክቫህ አስነብቧል።
  1. የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር በማህበራዊ ሚድያ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የከተማዋን ሰላም ለማወክና ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ግጭት እንዲነሳ ሲሰሩ የከረሙ ግለሰቦች ላይ ህግ የማስከበርና ሀሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ግለሰቦች ላይተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል። አስተዳደሩ “አንዳንድ ግለሰቦች በቦዲቲ ከተማ ውስጥ የከተማዋን ህዝብ በተለይም ወጣቱን የማይወክል ዕኩይ አጀንዳ በመያዝ ከተማዋን የሁከት ቀጠና ለማድረግ ለረጅም ጊዜ ሲያሴሩ ቢቆዩም ከእኩይ ምግባራቸው መለስ እንዲሉ በተለያዪ ጊዜያቶች በምክርና በተግሳጽ ፀጥታ አካላት ሊያሳልፉ ቢሞክሩም ግለሰቦቹ ከእኩይ ምግባራቸው መመለስ ተስኗቸው ዕኩይ ዓላማቸውን ሲከውኑ ቆይተዋል። በመሆኑም በህገ ወጥ መንገድ በከተማዋ ውስጥ በተለይም በማህበራዊ ድህረ ገጽ ላይ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ የፀጥታ ሀይል እርምጃ መውሰድ ጀምሯል” ብሏል።
  1. በካፋ ዞን ቢጣ ወረዳ ፍተሻ ከተደረገባቸዉ 309 የትምህርት መረጃዎች 115 ሀሰተኛ የትምህርት መረጃዎች መገኘታቸዉ የወረዳዉ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍን በፍቃዱ ገለፁ። አቶ መስፍን እነዚህ ባለ ሀሰተኛ መረጃ ሠራተኞች ከዚህ ወር ጀምሮ ደመወዝ የማያገኙና በቀጥታ ከስራቸዉ እንዲሰናበቱ የሚደረግ መሆኑን ገልፀው የስነምግባር ኦፊሰሮችን አክሎ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሀብት አስተዳደር ጽ/ቤት እንዲሁም እያንዳንዱ የሚመለከታቸዉ ተቋማት ህጉን በተከተለ መልኩ ይህንን ተግባር እንዲያስፈፅሙ በማሳሰብ በቀጣይም እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
  • በዚህ ሳምንት ያቀረብናቸው መረጃዎች እና የቴሌራም ሊንኮቻቸው:

– በሰኞ መልዕክታችን ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ ሀሠተኛ አካውንቶችን በተመለከተ ምን ማድረግ እንደምንችል አንድ ፅሁፍ አስነብበናል: https://t.me/ethiopiacheck/1474

– ሀሙስ እለት በአርቲስት ሌንጮ ገመቹ ስም የተከፈተ ሀሰተኛ የፌስቡክ ገፅን በአፋን ኦሮምኛ ዳስሰናል: https://t.me/ethiopiacheck/1476

– በተጨማሪም የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይንም ግጭቶች ሲኖሩ ስለሚበራከቱ ሰበር ዜናዎች (https://t.me/ethiopiacheck/1477) እና በተቀናጀ መልኩ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ስለሚሰራጩ ፕሮፖጋንዳዎች (https://t.me/ethiopiacheck/1478) አስነብበናል።

– በመጨረሻም፣ “ሀሰተኛ መውደዶች (Likes) ምንድን ናቸው? ምን አይነት ጥንቃቄዎችን ማድረግ አለብን?” የሚል ቪድዮ ሰርተን አጋርተናል: https://t.me/ethiopiacheck/1479)

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::