የአርብ የሚድያ ዳሰሳ

ሐምሌ 01/2014

1. አጭበርባሪዎች የግለሰቦች ስልክ ላይ በመደወል እና ከባንክ እንደደወሉ በማስመሰል ሽልማት ደርሷችኋል፣ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎታችሁን አስተካክሉ እና ሌሎች መሰል መልእክቶችን በማስተላለፍ ገንዘብ ለማጭበርበር ሙከራዎችን እያደረጉ እንደሆነ ጥቆማዎች ደርሰውኛል ሲል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል። ግለሰቦች እንደዚህ ዓይነት መልእክቶች በሚደርሳቸው ወቅት አቅራቢያቸው በሚገኝ የባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ ከማረጋገጣቸው በፊት ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ በመጠንቀቅ እራሳቸውን ከአጭበርባሪዎች እንዲጠብቁ አገልግሎቱ አሳስቧል። 

2. ቻይና በማህበራዊ ሚዲያ ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመናገር የብቃት ማረጋግጫ እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ደንብ አውጥታለች። የቻይና ብሔራዊ የሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ረዕቡ እለት ይፋ ያደረገው አዲስ ደንብ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ የቀጥታ ስርጭት የሚያቀርቡ ተጽኖ ፈጣሪዎችን የሚመለከት ሲሆን ስለ ህግ፣ ጤና፣ ትምህርትና ፋይናንስ ትንታኔ፣ ማብራሪያና ሃተታ ለማቅረብ በዘርፉ የብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ያስገድዳል።  

3. ዩትዩብ ቻናሎች የደንበኞቻቸውን ብዛት (subscribers number) እንዳይታይ የሚያደርጉበትን አሰራር በሐምሌ ወር መጨረሻ ከአገልግሎት እንደሚያስወጣ አስታውቋል። ዩትዩብ ይህን እርምጃ የሚወስደው ከታዋቂ ቻናሎች ጋር ተመሳስለው የሚከፈቱ ቻናሎችን ተጠቃሚዎች በቀላሉ እንዲለዩ ለማስቻል መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም የታዋቂ ቻናሎችን ስም አስመስሎ ለመክፈት ተግባር ላይ በሚውሉ ልዩ ሆህያት (special characters) አጠቃቀም ላይ ገደብ መጣሉን ዩቱዩብ አስታውቋል። በቪዲዮች ስር የሚሰጡ አስተያየቶችም ከመጋራታቸው በፊት በቻናሉ አስተናባሪዎች ግምገማ የሚደረግበትን ስርዐት መዘርጋቱንም አስነብቧል። 

4. ..አ በ2021 .ም በዩናይትድ ኪንግደም በተፈጸሙ ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማጭበርበር ድርጊቶች 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ በአታላዮች እጅ መግባቱን ዩኬ ፋይናንስ (UK Finance) የተባለ ተቋም ያወጣው ሪፖርት አስነብቧል። ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ በአታላዮች እጅ የገባው በዓመቱ በተፈጸሙ 195,996 ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉ የማጭበርበር ድርጊቶች መሆኑ ተገልጿል። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲወዳደር የ27 ፐርሰንት ብልጫ አለው። 

5. ትዊተር ኩባንያ አካውንቶችን እንድዘጋ እንዲሁም ትዊት የተደረጉ ይዘቶችን እንድሰርዝ እያስገደደኝ ነው ሲል የህንድን መንግስት በፍርድ ቤት መክሰሱን የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል። ትዊተር ክስ የመሰረተው የሀገሪቱን ህግ ተላልፈዋል የተባሉ አካውንቶችና ይዘቶች ላይ እርምጃ እንዲወስድ በህንድ መንግስት ከታዘዘ በኋላ ነው። የህንድ መንግስት ከዓመት በፊት ትዊተር የራሱን መመሪያዎች ሳይሆን የሀገሪቱን ህግ መሰረት አድርጎ እንዲሰራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::