የአርብ የሚድያ ዳሰሳ

ሐምሌ 08/2014

  1. በሚቀጥለው ወር በኬኒያ የሚደረገው ምርጫን የተመለከቱ ሀሠተኛ መረጃዎችና የጥላቻ መልዕክቶች በፕላትፎርሙ እንዳይጋሩ የሚያስችል ስራ መጀመሩን ቲክቶክ አስታውቋል። ለዚህም ኬኒያ ላይ ብቻ ትኩረቱን የሚያደርግ መመሪያ ማውጣቱን ገልጿል። እንዲሁም የሚዲያ ንቃት ንቅናቄ ለመከወን በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማህበራት፣ ከመንግስት፣ ከሚዲያ፣ ከትምህርት ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መቀናጀት መጀምሩንም አስታውቋል። ከሳምንታት በፊት ሞዚላ ፋውንዴሽን ይፋ ያደረገው የጥናት ሪፖርት በቲክቶክ የሚጋሩ የጥላቻ መልዕክቶች ለኬኒያ ምርጫ ስጋት መሆናቸውን አስነብቦ ነበር።
  2. የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ፍርድ ቤት ናይጄሪያ ለሰባት ወራት በትዊተር ላይ ጥላው የነበረው እቀባ ህገወጥ ነበር ሲል ብያኔ መስጠቱን ኤኤፍፒ ዘግቧል። ፍርድ ቤቱ ናይጄሪያ በትዊተር ላይ ጥላው የነበረው እቀባ በሀሳብ ነጻነትና በዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አንጻር የቆመ ነበር ያለ ሲሆን ይህም ከአፍሪካ ቻርተርና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ጋር የሚጣረስ መሆኑን ገልጿል። ድርጊቱም ዳግመኛ እንዳይፈጸም ፍርድ ቤቱ አሳስቧል። የናይጄሪያ መንግስት በትዊተር ላይ እቀባ የጣለው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የማህበራዊ መገናኛ ዘዴው በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተጋራን መልዕክት ከሰረዘ በኃላ ሲሆን እቀባውም ለሰባት ወራት የዘለቀ ነበር። ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው አንድ የናይጄሪያ የሲቪክ ማህበር ነበር።
  3. የፌስቡክ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ በፕላትፎርሞቹ የሚጋሩ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በተሻለ ሁኔታ ማጣራት የሚችል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን የሚጠቀም ቴክኖሎጂ ማበልጸጉን ሰኞ ዕለት ይፋ አድርጓል። ይህ ስፊር (Sphere) የሚል መጠሪያ የተሰጠው ቴክኖሎጂ በሜታ ፕላትፎርሞች የሚጋሩ መረጃዎችን ትክክለኛነት ለመፈተሽ በአንድ ጊዜ በመቶ ሺህዎች ከሚቆጠሩ ማጣቀሻዎች ጋር እንደሚያመሳክር ተገልጿል።
  4. ሜታ የመጀመሪያውን ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱን በትናትናው ዕለት ይፋ አድርጓል። ሰማንያ ሶስት ገጾች ባሉት ሪፖርት ሜታ በ2020/21 ዓ.ም ሰራኋቸው ያላቸውን ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ክንውኖችን ያስነበበ ሲሆን የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የጥላቻ መልዕክቶችን ስርጭት ለመግታት ወሰድኳቸው ያላቸውን እርምጃዎች ዘርዝሯል።
  5. በመጨረሻም፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዲሱ የበጀት ዓመት በጥላቻ ንግግርና ሀሠሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ለማድረግ ስለማቀዱ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ሰኞ ዕለት ዘግበዋል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የዴሞክራሲ ተቋማት ተብለው በሚታወቁት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተርና የመገናኛ ብዙኃን የማሻሻያና የለውጥ ስራዎችን የተመለከተ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በ2015 የበጀት ዓመት በጥላቻ ንግግርና ሀሠሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::